Friday, November 28, 2014

የእስክንድር ነጋ ያገባኛል ባይነት!

                                                                                      (በበላይ ማናዬ)

‹‹መብቴን አሳልፌ አልሰጥም፤ የትም ብሆን ስለመብቴና ሀገሬ ያገባኛል፡፡ እዚህ ከሚጠይቁኝ ሰዎች ጋር የፈለኩትን ማውራት እችላለሁ፡፡ እናንተ ከፈለጋችሁ በር ላይ መልሷቸው እንጂ እኔ ጋር ከመጡ በኋላ ስለሀገሬ ከእነሱ ጋር መነጋገር መብቴ ነው፡፡ አዎ የትም ቦታ ብሆን፣ መቼም ቢሆን ስለ ሀገሬ ያገባኛል!››

ይህን ያለው ትንታጉ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ እስክንድር ነጋ ነው፡፡ እስክንድር ነጋን ካወኩት ወዲህ እንደዛሬ በኃይለ ቃል ሲናገር ሰምቼው አላውቅም፤ ወይም ትዝ አይለኝም፡፡ ዛሬ (ህዳር 19/2007 ዓ.ም) እኩለ ቀን ላይ እስክንድርን ልጠይቀው ቃሊቲ ተገኝቼ ነበር፡፡ ሆኖም ሁኔታው ሁሉ እንደማንኛውም ቀን አልነበረም፡፡ በር ላይ ስደርስ በርከት ያሉ የአንድነት ፓርቲ አባላት ሰሞኑን እያካሄዱት ያለውን የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ በማስመልከት እስክንድር ነጋን፣ አንዱዓለም አራጌን እና ሌሎችንም ሊጠይቁ በቦታው ተገኝተው ነበር፡፡

በጠዋት ቂሊንጦ የሚገኙ ወዳጆቼን ጠይቄ አብረውኝ ከነበሩ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ጋር ነበር ወደ ቃሊቲ ያመራሁት፡፡ ቃሊቲ የተገኘው ሰው ሁሉ መጠየቅ የሚፈልገውን ሰው እና ሙሉ አድራሻውን እያስመዘገበ ሳለ በመሐል እኔም እስክንድርን መጠየቅ እንደምፈልግ ነግሬ ተመዘገብኩ፡፡ ከትንሽ ቆይታ በኋላ ግን ስማችሁ ከዚህ ቀደም ያልተመዘገባችሁ አሁን መግባት አትችሉም መባሉን መዝጋቢ ፖሊሱ አረዳን፡፡ እኔ እና ትንሽ ሰዎች መግባት ስንችል አብዛኛው ሰው ግን መግባት እንደማይችል ተነገረን፡፡

በዚህ ሁኔታ እስክንድር ጋር ደርሰን ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ አንድ የአንድነት ፓርቲ አባል ሰሞኑን ፓርቲያቸው እስረኞችን በተመለከተ በማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ እየተሰራ ያለውን ስራ ለእስክንድር ያብራራለት ጀመር፡፡ እስክንድር በተለመደ ጥሞናው ሲያዳምጠው ቆይቶ፣ በግሉ የተሰማውን እና መሆን ቢችል ያለውን ነጥብ ተናገረ፡፡ በመሐል ወጣቱ የአንድነት አባል ወደ እስክንድር ጠጋ ብሎ ሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮችን ሲነግረው ድንገት አንድ የፖሊስ አዛዥ ጨዋታቸውን እንዲያቆሙና እስክንድር ወደ እስር ቤቱ እንዲገባ፣ ወጣቱ የአንድነት አባል ደግሞ ወደ ውጪ እንዲወጣ በትዕዛዝ ማጣደፍ ያዘ፡፡

ይህኔ እስክንድር ለስለስ ባለ አነጋገር ምንም እንዳላጠፋን በመግለጽ ፖሊሱ መረጋጋት እንዳለበት አስረዳ፡፡ የፖሊስ አዛዡ ግን ጭራሽ ብሶበት ወጣቱ በቶሎ እንዲወጣ አደረገ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ‹ፖለቲካ ማውራት አቁሙ› የሚል ሆነ፡፡ ይህን ተከትሎ እስክንድር ድንገት በኃይለ ቃል ተናገረ፡፡ ‹‹መብቴን አሳልፌ አልሰጥም፤ የትም ብሆን ስለመብቴና ሀገሬ ያገባኛል፡፡ እዚህ ከሚጠይቁኝ ሰዎች ጋር የፈለኩትን ማውራት እችላለሁ፡፡ እናንተ ከፈለጋችሁ በር ላይ መልሷቸው እንጂ እኔ ጋር ከመጡ በኋላ ስለሀገሬ ከእነሱ ጋር መነጋገር መብቴ ነው፡፡ አዎ የትም ቦታ ብሆን፣ መቼም ቢሆን ስለ ሀገሬ ያገባኛል! የማወራው ስለ ሰላማዊ ትግል፣ ስለህጋዊ ትግል ነው!›› አለ እስክንድር በስሜት ውስጥ ሆኖ፡፡

በግሌ እስክንድር እንዲረጋጋ፣ ሁኔታው ግን ያልተገባ እንደሆነ ገለጽኩ፡፡ ፖሊሱ ግን ሊረጋጋ አልቻለም፡፡ እስክንድርን ይዞት ሄደ፡፡ ‹‹በርቱ! እንቅስቃሴያችሁ ህጋዊና ሰላማዊ ይሁን እንጂ ትግላችሁን ቀጥሉ!›› ሲል እስክንድር ወደ እስር ቤቱ እየገባ ተናገረ፡፡ የፖሊስ አዛዡም ከእስክንድር ጋር የነበረንን ቆይታ ሰዓቱ ሳይደርስ ገታው፡፡ የእስክንድር ያገባኛል ባይነት አስደመመኝ፡፡ እስር ቤት ሆኖም፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም እስክንድር ስለ ሀገሩ እንደሚያገባው በስሜት ተናገረ፡፡ መብቱን መቼም ቢሆን አሳልፎ እንደማይሰጥ አስረገጠ፡፡

ስለ ያገባኛል ባይነት ሳስብ በጠዋት ቂሊንጦ ያገኘኋቸውን የዞን 9 ጦማሪዎች አስታወስኩ፡፡ ‹ስለሚያገባን እንጦምራለን!› ይላሉ ወጣቶቹ ጦማሪያን፡፡ ከአብርሃ ደስታ ጋር አብረው ያገኘኋቸው እነ በፍቃዱ ኃይሉ እና አጥናፍ ብርሃኔ ብዙ ጉዳዮችን እያነሱ አወጉኝ፡፡ ‹‹ህወሓት አንድ ወይም ሁለት ነባር የህወሓት ባለስልጣናትን በሽብር ከከሰሰ ስርዓቱ እንዳበቃለት እቆጥራለሁ፡፡ ምክንያቱም ሽብር ማታለያ መሆኑ ይቀራል›› አለኝ በፍቃዱ ኃይሉ፡፡ አብርሃ ደስታ ቀበል አድርጎ ‹‹እናት አልጋነሽ በሽብር ስትከሰስ በጣም ብዙ ሰው ተቃውሞ ነበር›› አለ፡፡ አጥናፍ በበኩሉ ‹‹ቄስና ሸህ ሽብርተኛ እየተባለ አይደለም እንዴ›› በማለት ጠየቀ፡፡

አብርሃ ደስታ አንድ ነገር በኃይል እንደሚቆጨው ተናገረ፡፡ ምን እንደሆነ ጠየቅሁት፡፡ ‹‹ብዙ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ሳላደርግ መታሰሬ ይቆጨኛል!›› አለ፡፡ በፍቃዱ በበኩሉ፣ ‹‹እኔም የገባኝ ነገር ያለውን የሰላማዊና ህጋዊ የመስሪያ ልክ አለመስራታችን ነው፡፡ አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው እንዲህ ለሚያስሩን ስንት ህጋዊና ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን እንኳ ሳናደርግ በትንሽ ነገር በርግገው እዚህ ሲያስገቡን ይቆጨኛል›› በማለት ሀሳቡን ቀጠለ፡፡ ‹‹በእርግጥ አንድ ሰው አሁን መጠንቀቅ ያለበት የሚሰራው ስራ ህጋዊ መሆን አለመሆኑን እንጂ፣ ይህን ካደረኩማ ያስሩኛል የሚለውን መሆን የለበትም፡፡ እነሱ ከፈለጉ ያስሩሃል፤ ስለዚህ መብትህን ተጠቅመህ መታሰሩ ይሻላል እንዲሁ ምንም ሳይሰሩ ከመግባት›› ሲል አብርሃ ሀሳቡን አካፈለ፡፡

ቂሊንጦ ከእነ በፍቃዱ ጋር ስንጨዋወት ስለእስክንድር ነጋ ትሁትነት፣ አስተዋይነት፣ ሰላማዊነት እያነሱ ሰላምታ እንዳደርስላቸው ጠየቁኝ፡፡ እኔም እስክንድር ነጋን ሳውቀው በትሁትነቱ፣ በአስተዋይነቱና በሰላማዊነቱ ነው፡፡ ዛሬ በነበረው ሁኔታ ግን ክፉኛ ተበሳጭቶ ነበር የተመለከትኩት፡፡ ያ ፈገግታው ከፊቱ ብን ብሎ ጠፍቶ ‹‹ያገባኛል!›› ሲልበት የነበረውን ስሜት ግር አለኝ፡፡ ካልነኩት የማይነካ ሰው ሲነኩት ትንታግ ነው፡፡ እስክንድር እዛ ስሜት ውስጥ የገባው ተገድዶ ነበር፡፡ ሊጠይቁት የመጡትን ሰዎች አብዛኞቹን አላስገባም ማለታቸው ሳያንስ ከገቡትም መካከል የምታወራውን እኔ ልምረጥልህ በሚል ግብዝነት አባርረዋል፡፡ እስክንድር ይህን አይቶ ዝም ማለት አልቻለም፡፡ ስለሆነም እንዲህ አለ፤

‹‹…እዚህ ከሚጠይቁኝ ሰዎች ጋር የፈለኩትን ማውራት እችላለሁ፡፡ እናንተ ከፈለጋችሁ በር ላይ መልሷቸው እንጂ እኔ ጋር ከመጡ በኋላ ስለሀገሬ ከእነሱ ጋር መነጋገር መብቴ ነው፡፡ አዎ የትም ቦታ ብሆን፣ መቼም ቢሆን ስለ ሀገሬ ያገባኛል! የማወራው ስለ ሰላማዊ ትግል፣ ስለህጋዊ ትግል ነው! ስለሀገሬ ያገባኛል!››

Thursday, November 27, 2014

ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በኖርዌይ ኦስሎ ተካሄደ!!!

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌ የወጣቶች ክፍል አዘጋጅነት በዛሬው እለት ሀሙስ (November 27,2014)  በኖርዌ ኦስሎ በእንግሊዝ ኢንባሲ ፊት በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሩቅም ከቅርብም በአንድነት በመሰባሰብ ከቀኑ 13፡30 እስከ 15፡00 ስዓት ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ።
የሰልፉ ዋና አላማ የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሃፊና የሰባዊ መብት ተቆርቋሪ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ  በአንምባ ገነኑ የወያኔ ቡድን በህገ ወጥ መንገድ ታፍነውና ፍትህ ተነፍገው በእስር ቤት መታሰራቸውን ለመቃወም ሲሆን በሰልፉ ስፍራ የተገኙ ሰዎች ሁሉ አቶ አንዳርጋቸው ለዲሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት መከበር ከወጣትነት ጀምሮ የታገለ ታላቅ የሰላም ምሳሌ፣ የፍትህ ተምሳሌት፣ የነጻነት በር ከፋች እንዲሁም አገራዊ ስሜት የተላበሰ አርበኛ እንጂ እስር፣ ድብደባና መሰቃየት የሚገባው ሰው አልነበረም በማለት ለእንግሊዝ መንግስት በኢንባሲው አማካኝነት ዜጋዋን ከአረመኔና ጨካኝ መዳፍ እንድትታደግና ፍትህ እንዲያገኝ  በከፍተኛ ድምጽ አሳስበዋል።
ወጣቶች እጃቸውን በሰንሰለት በማሰር እኛም እንደ አርበኛው አንዳርጋቸው ጽጌና በእስር ቤት የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውን የቁም እስረኞች ነን የሚል ጥልቅ መልእክት አስተላልፈዋል። ብዙ መስራትና መጻፍ የሚችሉ እጆች፣ መናገር የሚችል አንደበት፣ የእውቀት ባለቤት የሆነ አእምሮ ታስረዋልና እኛም ወጣቶች እስረኞች ነን በሚል ውስጣዊ ስሜት ለስዓታት የኖርዌ ብርድና ቁር ሳይበግራቸው እጃቸውን በሰንሰለት በማሰር ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል።
እንዲሁም ሰልፈኞቹ  የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ በታላቅ ድምጽና ስሜት ለኢንባሲው  አሰምተዋል።  ከአሰሟቸው  መፈክሮች መካከል ለአብነትUK, were is your citizen, Free Andrgachew Tsige, Andargachew is our icon of democracy, where is your action , stop discrimination among citizens, Yes, we are all Andrgachew Tsige, Brtain don't support terrirost regim in Ethiopia” የሚሉት ይገኙበታል::
ሰልፎኞችም የኢንግሊዝ  መንግሥት የነጻነት ታጋዩን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ከወያኔ እጅ እስካላወጡ  ድረስ ተቃውሞው ቀጣይ እስከ መጨረሻው ድረስ ከዚህ በበለጠ ቁጣና እልህ በተሞላበት ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ ተናግረዋል።  በተመሳሳይም ለአንዳርጋቸው ያላችውን ፍቅርና ክብር በአደባባይ አስመሰክረዋል። 
በመጨረሻም በድርጅቱ የተዘጋጀውን  ደብዳቤ በድርጅቱ ሊቀመንበር በአቶ ዮሃንስ ዓለሙ  አማካኝነት ለእንግሊዝ ኢምባሲ ተወካይ ጉዳዩ ትኩረት የሚሻና ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን ለማሳሰብ ቢፈለጉም ተወካይ ሊመጣ ባለመቻሉ ደብዳቤው በበር ጠባቂው አማካኝነት እንዲደርሳቸው ተደርጓል። በተጨማሪም ደብዳቤውን በኢሜይል በድጋሚ እንደሚላክ ለሰልፈኞች አሳውቀዋል። ወደፊት በሚደረገው ተቃዉሞ ላይ ተወካይ መጥቶ እስካልተቀበለንና አቶ አንዳርጋቸው የደረሱበትን እስካላወቅን ድረስ ከኢንባሲው በር የማንቀሳቀስ መሆኑን ሁሉም በከፍተኛ ድምጽ አሰምተው ዝግጅቱ በተሳካ ሁኔታ ከቀኑ 1500 ተጠናቋል።

በአጠቃላይ እንዲህ አይነት ሰላማዊ ሰልፍ እና መሰል ተቃውሞዎች በወጣቶች አስተባባሪነት መካሄዱ ለተተኪው ትውልድ  ኃላፊነትና አገራዊ ስሜት እንዲሰማው በጎ አስትዋጾ ስለሚያደርግ ሊበረታታ እና ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል። ወጣቱ ትውልድ አገር ተረካቢ እንደመሆኑ መጠን የአገሩን ታሪክ ተገንዝቦ ወያኔን በቃህ፣ በህዝብና ለህዝብ የቆመ መንግሥት በዲሞክራሲ መንገድ ለአገራችን ያስፈልጋታል በማለት እምቅ ኃይሉን ማሳየት ይኖርበታል።
ወጣት ሁሉን ነገር የመለወጥ ኃይልና አቅም አለው!አምባገነን መንግሥትን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት .....................አንድነት ህብረት ከአለን መቀየር እንችላለን!   

ዛሬም ነገም ሁላችንም አንዳርጋቸው ፅጌ ነን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
Source 

  DCESON

Friday, November 7, 2014

ወጣትነትና አስትዋጾው


የአንድ አገር ቀጣይነት ያለው እድገት የሚለካው በአላት ሃብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን ያንን ተረክቦ በአደራ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚችል ትውልዳዊ ትስስር ሲኖር ነው። ይህንንም እንደ ድልድይ ሆኖ  ከአንዱ ትውልድ ወደቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፈው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው። በማንኛውም አገር፣ ጊዜና ዘመን እያንዳንዱ ተተኪ ትውልድ የአገሩ ወራሽ፣ ተተኪና ተረካቢ፣ ጠባቂና ለሚቀጥለውም ትውልድ የማውረስ፣ የማስተላልፍና የማስረከብ ኃላፊነትና ግደታ  አለበት። አገርን ከእነ ሙሉ ክብ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ከወጣቱ የዜግነት ግደታ ነው። አገር አንድና ሁለት ትውልድ ብቻ የሚቆምና የሚያልፍ ሳይሆን ማያቋርጥ ቀጣይነት ያለው ትውልድ ሁሉ የሚቀባበለው፣የሚጠብቀው ያለፈውንና የሚመጣውን ትውልድ ሁሉ የያዘና ያቀፈ የአገርና ሕዝብ የታሪክ ሂደት ነው።
ወጣት ለአንድ አገር በሦስቱም ዘርፍ ማለትም በማህበራዊ፣ በሥነ ምጣኔ ሃብታዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርጋል። ለዚህም ነው ወጣት ለአንድ አገር የጀርባ አጥንት ነው የሚባለው።

ወጣትነት፦ ወጣትነት ማለት በሰው ልጅ ሥነ ሕይወታዊ ምዕራፍ አንድን የእድሜ ክልል የሚወክልና የተለያዩ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊ፣ አካላዊ አቋምና ደረጃ ያለው ነው።  አገራት ከራሳቸው ማህበራዊ፣ ባህላዊና ሌሎች እሴቶችን መሰረት በማድረግወጣትነት የሚሰጡት የእድሜ ክልል ይለያያል። ለምሳሌ፦ አውሮፓ 15—30 አፍሪካ 15_35 ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል ይወክላል።
በዚህ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች የወጣትነት መገለጫወች/ምልክቶች ይታዩባቸዋል፤ ለውጦችም በከፍተኛ ደረጃ የሚከሰቱበት ነው። ማለትም አካላዊ/physical ስሜታዊ/emotional አዕምሮአዊ/cognitive እውቀታዊ/ knowledge ጥበባዊ/ skill እና መስተጋብራዊ/relationships ወጣትነት ከእነዚህ ከፍተኛ ለውጦች ጋር በተያያዘ እራስን ለማወቅ የሚደረገው ጥረት በጣም ከፍ የሚልበት፣ ለችግር ተጋላጭነት የሚጨምርበት፤ አንድን ነገር በማድረግ በሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ለማትረፍ የሚሮጥበት እንጂ በሚደረገው ነገር የሚፈጠረው መጥፎ  ነገር በውል የማይጤንበት ጊዜ ነው። በዚህ ወቅት ከፍተኛ ጾታዊ ፍላጎት የሚቀሰቀስበት እና የወጣቶች አዕምሮ የሚባክንበት፤ ለልዩ ልዩ ሱሶች የሚጋለጡበት፤ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚሉበት ወዘተ ጊዜ ነው። ወጣትነት የእድሜ ዘመን ጠቃሚም ጎጅም ምልክቶች ይታዩብናል። ከእነዚህም መካከል የዳበረ አካላዊ ብቃት፣ተለዋዋጭ ስሜት፣ በራስ መተማመን/መመካት፣ ገደብ ማጣት/ገደብን አለመቀበል፣ በልጦ መታየትና ፈጣንነት ናቸው።
በተለይ ሁሉንም ነገር ለማየት፣ ለመፈተሽ፣ የመቅመስ ስሜት የሚታይበት ነው። ክፉውንም መልካሙንም፣ የሚጠቅመውንም የማይጠቅመውንም ለመለየት ማየት፣ ማድረግና መሞከር የሚፈለግበት ዘመን ነው። እንዲሁም የወጣትነት ዘመን ከሁሉ በእውቀትም፣ በኃይልም፣ በውበትም፣ በሙያም፣ በችሎታም የምበልጠውና የምሻለው እኔ ነኝ የሚባልበት ጊዜ ነው። የተሻለ ሁኖ ለመገኘት የመፈለግ ስሜት የሚታይበት ነው። ለምሳሌ, ከሌሎች መካከልተውቦ ለመገኘት፣ ተናግሮ ለመደበጥ/ለማሳመን፣  ጽፎ ለማስነበብ፣ አሸንፎ ለመሞገስ በአጠቃላይ አይነ ግቡ ሁኖ ለመገኘት የሚደከምበት ዘመን ስለሆነ ወጣትነት በአግባቡ ከአልተያዘ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው።
በአጠቃላይ የዘመኑን ወጣት ለአገሩ በአለው አመለካከት በሦስት መክፈል ይችላል።
  1. ወጣትነትን ተጠቅሞ ለአገሩ የሚያስብ የሚጨነቅ፣ አገራዊ ስሜት ፍቅር ያለው፣ የለውጥ ኃይል የሆነ፣ ለነጻነትም የሚታገል፣ለአገር እድገትና ዲሞክራሲ ግንባታ የሚፋጠኑ
  2. አገሩን የማያውቅ፣ ማንነቱን የረሳ፣ ማዎቅም የማይፈልግ፣ ለጠቅም ብቻ የሚጓዝና ተስፋ የለሽ ወጣት
  3. በስሜት የሚጋዝ፣ አንዴ አገር ወዳድ ይሆናል፣ ወደነፈሰበት የሚጋዝ፣ ዓላማና ግብ የሌለው
አገር እና ዲሞክራሲ ሲባል
አገር ዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት አንድ አገር ፣ ሉዓላዊ አገር  ለመባል  ሦስት መሰረታዊ ነገሮች ያስፈልጓታል። ከእነዚህ መሰረታዊ ነገሮች መካከል አንዱ ከተነካ ሉዐላዊት አገር የሚለው ይቀርና ሌላ ስም ይሰጣታል። እነዚህ ሦስቱም ተደጋግፈውና አንዱ የአንዱን ሉዐላዊነት መጠበቅ፣ ማስጠበቅ ይኖርበታል። አንዱ አንዱን ካጣ ምዕሉ ሊሆን አይችልም። የአንድ አገር ሦስቱ መሰረታዊ ነገሮች የሚባሉት ግዛት፣ ህዝብና መንግስት ናቸው። እንዲሁም ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችን አንድ የሚያደርጋቸውና ከፍ አድርገው የሚያውለበልቡት የአንድ ሀገር መለያ ባንዲራ/ሰንደቃላማ ሲኖራት ነው። 
ግዛት፦ የአንድ አገር ግዛት ማለት ወሰኗ፣ ድንበሯ፣ የቆዷ ስፋቷ፣ በውስጧ የየያዘዛቸው ወንዝ፣ ተራራ፣ሸለቆ፣ ባጠቃላይ ሙሉ ካርታዋ ማለት ነው። የኢትዮጵያ ግዛት ስንል በምስራቅ፣ በሰሜን፣ በደቡብና በምዕራብ ከሚያዋስኗት ግዛቶች የምትለይበት ቦታ፣ ድንበር ወይም ክልል ጀምሮ በውስጧ የየያዘዛቸው ወንዝ፣ ተራራ፣ሸለቆ ወዘተ ሙሉ የቆዳ ስፋቷን ያዋስናል። ከዚህ የቆዷ ስፋቷ ትንሽ ከተነካ ግን የነበራት ሙሉ ግዛት አይኖራትም። መንግሥት ለግዛቷ ሲጨነቅ አናይም። እንደ ጥሬ እቃ ግዛቷን ሲሸጥም፣ ሲደራደርባትም እናያለን። ይህን ግዛቷን ለማስጠበቅ ወጣቱ  በመተባበርና በመጠበቅ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት።
ለሕዝብ፦ ከሁሉም በላይ ክብርና ሥልጣን ሊሰጠው የሚገባ ነው። ሕዝብ ከሌለ የምንላቸው ነገሮች የሉም። ህዝብ ከሌለ ለግዛት ስም ጠርቶ፣ ወሰን ወስኖ ሊያስቀምጥ የሚችል አካል የለም። ስለዚህ ሕዝም ውድ ዋጋ ያለው ነው። በሌላም በኩል ፈጣሪ አክብሮና ባለ አዕይምሮ አድርጎ የፈጠረው መተኪያ የለለው ፍጡር ነው። ስለዚህ ግዛት በሕዝም ይከበራል፤ መንግሥት ደግሞ በሕዝብ ይከብራል/ይነግሣል። ላከበረው፣ ላነገሠው ሕዝብ መንግሥት ዋጋ ሊከፍልለት ይገባል። ከዚያ ውጭ ግን(የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ፀንቶ፣ ታየ ህዝባዊነት ዳር እስከዳር በርቶ)እያልን የአገር መለያ፣ የማንነታችን መገለጫ የሆነውን ባንዲራ እያውለበለብን የምንዘምረው የህዝብ መዝሙር ከንቱና ዋጋ አልባ ሆኗል ማለት ነው። ባንዲራ ደግሞ ጨርቅ አይደለም ልዩ መለያ ማንነታችን ነው። ይህን የማንነት ጉዳይ ሊያስከብረው የሚችል ደግሞ ህዝብ ነው። ሕዝብ ማለት ደግሞ እያንዳንዳችን ስብስብ/ድምር ውጤት ነው። ስለዝህ ለህዝብ የሚያስፈልገውን ነጻነት፣ እድገት፣ብልጽግና እንዲያገኝ እኛ ወጣቶች የበኩላችንን ድርሻ መወጣት አለብን፤ ግዴታችንም ነው።  
መንግሥት፦ መንግሥት ማለት በጥሬ ትርጉሙ በአንድ አገር  ውስጥ ሕጎችን ለማውጣትና ለማስፈጸም፣ ሕዝብን ለማስተባበርና ደኅንነቱን ለማስጠበቅ፣ አገርን ለማስከበር  ስልጣንና ኃላፊነት ያለው አካል ማለት ነው። እንዲሁም በምርጫም ይሁን በሌላ መንገድ በሕዝብ ድጋፍ ስልጣን ላይ የወጣ አካል ነው። ስለዚህ ይህ በሕዝብ ድጋፍ ሥልጣንን የያዘ አካል ከስሙና ከትክክለኛ ትርጉሙ አንፃር ለህዝብና ለአገሪቱ ግዛት ከማንም በላይ የሚጨነቅ፣ የሚያስብና የሚቆረቆር አካል መሆን ይኖርበታል ምክንያቱም ሕዝብ ከሌለ መንግሥት የለም፤ ግዛትም ከሌለ እንዲሁ። ከምንም በላይ ለመንግሥት መኖር ሁለቱም ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው። የየትኛም አገር መንግሥት ይህን ተገንዝቦ ለሁለቱም የሚገባውን እንክብካቤና ክብር መስጠት ካልቻለ የመኖር ዋስትናው ጥያቄ ውስጥ ይገባል። አወዳደቁም በእጅጉ የከፋ ይሆናል። 
ዲሞክራሲ፦ ማለት የዲሞክራሲ ጥንታዊ ትርጉም “ የህዝብ ሃይል” ወይም “ የህዝብ አስተዳደር” ሲሆን መሰረቱም ሁለት የግሪክ ቃላቶች ዴሞስ(demos)“ህዝብ” እና ክራቶስ (kratos)“ሃይል” ውህደት ነው:: የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት በነበሩት አብረሃም ሊንከን አተረጓጐምም መሰረት ደግሞ ዲሞክራሲ ማለት በህዝብ የተመረጠና ለህዝብ የቆመ የህዝብ መንግስት ማለት ነው:: በዚህ ዓይነት ስርዓት ውስጥ የተመረጡ መሪዎች ቀጥተኛ ተጠሪነታቸው (accountability) ለህዝቡ ሲሆን የሚሰጡት አገልግሎትም በህዝቡ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ብቻ እንደሆነ ይገለጻል:: ዘመናዊው የዲሞክራሲ ምንነት በቀደምቶቹ ትርጉሞች ላይ የዳበረ ሲሆን የሰው ልጅ መሰረታዊና ፖለቲካዊ መብቶች የማክበር፣ በህዝቦች መካከል የሰፈነ እኩልነት፣ ነጻና ፍትሃዊ የመምረጥና የመመረጥ መብት ያለው፣ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ የሚፈቅድ፣ እንዲሁም ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ የሆነ የፍትህ ሥርዓትንና ነጻ ፕሬስን ያካተ ተቋም መሆን እንዳለበት ይታወቃል።
ኢትዮጵያ አገራችን ብዙ  መንግሥታትን ያስተናገደች አገር ናት። ሆኖም ግን ለዘመናት ታሪኳን፣ ባህሏን፣ እምነቷን፣ አንድነቷን፣ ድል አድራጊነትን እና ዳር ድንበሯን ጠብቃ አስጠብቃ  የኖረች እና መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ እንግዳ ተቀባይነትን፣ ዘርንና ጎሳን መሰረት ሳታደርግ ለዘመናት የቆየች የጀግኖች አገር ናት። 

ዛሬ መንግሥት ነይ ባዩ የወያኔ/ሕወሓት ቡድን ግን፦
  • ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳትኖር የሚፈልግ፣  አገራዊ ስሜት ፈጽሞ የማይታይበት፣ ህዝቧና አገሪቱን የድህነት ሰለባ አድርጎ ከመኖር ወደ አለመኖር ዳርጎናል።
  • ትውልድ ገዳይ/ ወጣት አልባ /አገራዊ ስሜት እንዳይኖረን/ከሥርዓተ ት/ቱ ጀምሮ
  • የሰባዊ መብት ጥሰትና ረገጣ በግንባር ቀደም የሚጠቀስ፣ ከራሱ ቡድን ውጭ ሰው እንደሰው የማይቆጠርበት አገር አድርጓታል።
  • ተፈጥሮአዊና መሰረታዊ መብት የማምለክ፣ የመንቀሳቀስ፣ የመሥራት፣ የመኖር ነጻነታችንን ነፍጎናል፤
  • ዲሞክራሲያዊ መብታችን የመደራጀት፣ የመቃወም፣ የመወያየት፣ የመምረጥ  ወዘተ በዲሞክራሲ ስም ፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት፣ ፀረ ዲሞክራሲ፣ ፀረ ህግ ተብሎ በፀረ ሽብር ህግ አማካኝነት አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የሚገደሉበት፣ የሚታሰሩበት፣ የሚንገላቱበት፣ የሚደበደቡበት፣ የሚሰደዱባት አንዳርጋቸው ጽጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታየ፣ አንዷለም አራጌ፣ ርዮት ዓለሙ፣ ጦማርያን፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሳይቀሩ
  • ልማት ወያኔ በተግባር ሳይሆን በቃል ብቻ 11% ማደግ፣ አገርን መሸጥ እና ሰባዊ መብትን ከመገንባት ይልቅ ህንጻና መንገድ መገንባት ማለት ነው። 
ይህን ጨቋኝና አፋኝ ሥርዓት አሶግዶ አገራዊ ስሜት ለመላበስ እንዲሁም ለአገር እድገትና ዲሞክራሲ ግንባታ የወጣቱ አስትዋጾ ከፍተኛ መሆኑን ተረድቶ ለነጻነት መታገል የእያንዳንዱ ወጣት አገራዊ ግዴታም ኃላፊነትም ነው።
አገራዊ ስሜት መላበስ ሲባል አገርን በሚገባ ማወቅና በማነኛውም መልኩ ለችግሯ ደራሽና ተቆርቋሪ መሆን ማለት ነው። ለባንዲራዋ ክብር መስጠት ነው። ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ መገንዘብ ነው። ወያኔ ወጣቱን ስለአካባቢው እንጂ እንደ አገር ማውራት እንዲያቆም አድርጎናል። ስለ ኢትዮጵያ ሲወራ እንደ ሁለተኛ ሦስተኛ ዜጋ ሁነን ቁመን የምንሰማ በርካቶች ሁነናል። ትርጉሙም ስሜቱም ጠፍቶብናል። ወጣቱም ብሔርን፣ ቋንቋን ይሰብካል። የፖለቲካ ድርጅቶችም ይህንኑ ያስተጋባሉ። ለአገር ሳይሆን ለብሔር ብቻ የቆሙ ናቸው። ይህን ከባድ ችግር አሶግደን አገራዊ ስሜት ሰንቀን ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ ከተረዳን የወያኔ ቡድን አሁን በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን ችግር ማስቆም እንችላለን። አገራዊ ስሜት በውስጣችን ከነገሰ ለአገር፣ ለወገንና ለክብራችን ዘብ እንቆማለን።

አገራዊ ስሜት ያለው ወጣት ከሌሎች የሚለዩበት፦
  • ፍቅር ...ሰባዊና አገራዊ ፍቅር፣ ለሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ክብርና ፍቅር መስጠት።
  • ተስፋ ...ለተተኪ ትውልድ አርቆ ያስባል፣ መልካም ነገሮችን በተስፋ መነጸር መመልከት ይችላል፣ ተስፋ ኃይልና ብርታት ይሆናል፣ በተስፋ የነጻነት፣ የፍትህና የዲሞክራሲ ብርሃን ማየት ይቻላልና።
  • ግልጽነትና ተጠያቂነትን ገንዘብ ያደርጋል, የሚሰራውን ተግባር በግልጽና በተጠያቂነት ያከናውናል፣ ለሥራው ሁሉ ለራሱ፣ ለአገሩና ለወገኑ ተጠያቂ ይሆናል። 
  • ሙስናን ፈጽሞ ይጠላል፣ ያጋልጣል/ይቃዎማል።
  • መልካም ሥነ ምግባር የተላበሰ/ ከማይጠቅም ነገር እራስን ያርቃል። 
  • የአገርን ግዛቷን፣ ታሪኳን፣ ባህሏን መጠበቅ መመስከር፤ ለአገሩ ደራሽና ተቆርቋሪ ነው።
  • እራስን ሁኖ መኖር ይችላል፣ ማንነቱን ጥንቅቆ ያውቃል፣ በማንነቱም ይኮራል።
  • ነጻነት፣ ለፍትህና ለዲሞክራሲ እየታገሉ ምሳሌና አርያ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ይከተላል።
አገራዊ እድገትና ዲሞክራሲ ለማስፈን ወጣቱ ሊከተላቸው የሚገቡ ነገሮች
  1. ዓላማ፦ በመጀመሪያ ከስሜት ወጠን ዓላማና ግብ ሊኖረን ይገባል።  ምን እንደምንሰራ እና የት ለመድረስ የሚሉትን ነገሮች ከመጀመራችን በፊት በሚገባ ማዎቅና መገንዘብ፣ 
  2. ቆራጥነት፦ ዓላማችንን ከግብ ለማድረስ ቆርጦ መነሳት ያስፈልጋል። ፈራ ተባ ማለት ለውጠት አያበቃም። ወጣትነት ኃይል፣ጉልበት አለንና። 
  3. እውቀት ገብየት፡ በቆራጥነት ለተነሳንበት ዓላማ በቂ እውቀት ያስፈልገናል። ስለ ታሪካችን፣ ባህላችን፣ማንነታችን እውቀት ያስፈልጋል። በቅኝ ግዛት በተገዛን ኑሮ  የሚል ወጣት ይሰማል ከእውቀት ማነስ የተነሳ፣ የቅኝ ግዛት ምንነትና አስከፊነት ባለመረዳትና አባቶቻችን ለምን ሰማዕትነትን እንደተቀበሉ ካለመረዳት።.ስለዚህ ለሁሉም ነገር እውቀት አስፈላጊ ነው። እውቀትን ከህይወት ተሞክሮ፣ ከት/ት፣ ከመልካም ጋደኛ፣ ከቤተሰብ፣ ከታላላቅ ሰዎች እንቀስማለን።
  4. ስልታዊ ዕቅድ መንደፍ፦ በአገኘነው እውቀት ተጠቅመን ሊያዋጣና ሊያስኬድ የሚችል ስልት፣ ሁለገብ የትግል ስልት መንደፍና መከተል። ከዓላማችን ሊያደርሰን የሚችል ወቅታዊና ዘላቂ እድገትን፣ መብትን፣ ሰላምን፣ ሊያጎናጽፍ የሚችል ስልት መከተልና ውጤታማ ለመሆን መታገል እንደሚያስፈልግ ልንገነዘብ ይገባል።
  5. ነጻነትን ማዎጅ፦ ነጻነት የሚለውን ቃል ሰዎች የተለያየ አተረጓጎም ሊሰጡት ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ነጻነት ማለት ከግዞት መውጣት፤ ከሌሎች ተጽኖዎች መውጣት፤ በራስ መወሰን ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ማንም ሌላ ሰው ሳያስገድደን እና የማንንም መብት ሳንነፍግ በነገሮች ላይ በራስ ወይም በጋራ መወሰን መቻል ነው፡፡ ደሞክራሲ ሊባልም ይችላል፡፡ ነጻነት አለ ካልን ሃሳባችን ወይም ተሳትፏችን ተሰሚነትና ተቀባይነት አለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ነጻነትን አውጀን  ለሰላም፣ ለፍትህና ለዲሞክራስ ቆርጦ  መነሳት ያስፈልጋል።
  6. አንድነታችን መጠበቅ፦  ወጣቱ ሊያከናውን ከሚገባው ነገር አንዱና ትልቆ ጉዳይ አንድነትን ብሄራዊነትን፣ አገራዊነትን ማምጣት ነው።ችግር ለመፍታትም ሆነ መፍትሔ ለመፈለግ እኛ አንድ መሆን ይኖርብናል። መግባባት፣ መነጋገር፣ መወያየት በምንችልባቸው ነገሮች ላይ አንድ መሆን አለብን። በአንድ አገር ውስጥ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣እምነት ያለው ህዝብ በአገሪቱ ግዛት አንድ መሆን መቻል አለብን። ይህንን ሊያስተባብርና ሊመራ እንዲሁም አንድ ሊያደርገን የሚችል መንግሥት ሊኖረን ይገባል። ከዚያ ውጭ በቋንቋ፣ በባህል፣ በእምነት እንደተለያየን ሁሉ አንድ ሊያደርገን የሚችል የጋራ የሆነ ነገር ከለሌን ችግሩን በህብረት መቅረፍም ሆነ መቀነስ አንችልም። ወያኔ/ህወሓት ብሔር፣ ጎሳ፣ ቋንቋ፣ እምነት እያለ ሊከፋፍለን፣ ሊለያየን አይገባም። ይህን ድርጊት የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የግል/ሰባዊ መብት ድርጅቶችና ሕዝብ ሁላችንም  ማውገዝና ማስቆም ይኖርብናል። በተለይ ወጣቱ ትውልድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት።
በአጠቃላይ የወጣቱ አስትዋጾ ዘርፈ ብዙ ነው፤ በዚህ ወይም በዚያ ብሎ መወሰን ከባድና አስቸጋሪ ነው። የለውጥ ኃይል እስከሆነ ድረስ በሁሉም ዘርፍ መገኘት እና አገርን ወደተሻለ ደረጃ ማድረስ የዜግነት ግዴታ አድርጎ  መውሰድ ይኖርብናል።
 በማነኛውም መልኩ አገራችንን ለማገልገል እራሳችንን ብቁና ዝግጁ ማድረግ ይገባል።ለአገር እድገት፣ ለነጻነት፣ ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲ ግንባታ የወጣቱ አስትዋጾ ከፍተኛ መሆኑን ተረድተን በምንችለው ሁሉ የበኩላችንን ኃላፊነትና ግዴታ መወጣት አለብን። መንግሥት ነኝ ባዩን የህወሓትን ቡድን በቃህ መብትና ህግ ይከበር ብለን በአንድነት መነሳት አለብን